የገብር ኄር ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ተከበረ

በገብር ኄር የጤናና ማኅበራዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ለመጀመርያ ጊዜ የገብር ኄር ሳምንት በልዩ ልዩ መርኀ ግብራት ሲከበር ሰንብቷል፡፡ ገብር ኄር- ታማኝና ቅን አገልጋይ- በሚል መርኅ ላይ ተመርኩዞ በሳምንቱ የተለያዩ ክንውኖች በድርጅቱ አስተባባሪነት ተካሂደዋል፡፡ በዚህም ስለ በጎነት ግንዛቤ መፍጠር፣ የተለያዩ ተቋማት የነጻ ወይም የቅናሽ አገልግሎት እንዲሰጡ ማበረታታትና የደም ልገሣ ማካሄድ ዋና ዋናዎቹ ክንውኖች ናቸው፡፡


ገብር ኄር የጤናና ማኅበራዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ሰዎች ለሰዎች በጎን እንዲያደርጉ ሁሉም በተሰጠቸው መክሊት እንዲያተርፉ ተቋማት ውይይት እንዲያደርጉ በመጋበዝ እንዲሁም ድርጅቱ በራሱ መርኀ ግብር አዘጋጅቶ ግንዛቤ በመስጠት ሳምንቱን ዘክሯል፡፡ ግንዛቤውን በተቋማት ለማስፋትና ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ለማሳሰብ የገብር ኄር ሳምንት ማስጀመሪያ መርኀ ግብር አርብ መጋቢት 23፣ 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 11፡30 እስከ 2፡30 በቀነኒሳ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ በዚህም መርኀ ግብር ልዩ ልዩ እንግዶችንና ምኁራንን በመጋበዝ ንግግር ፣ ግጥምና ዲስኩር ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም በዶ/ር ናትናኤል ታዬ- የገብር ኄር ቦርድ ሰብሳቢ- ስለ ገብር ኄር የጤናና ማኅበራዊ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት ማንነት፣ዓላማ፣ የሠራቸውና ሊሠራቸው ስላሰባቸው ሥራዎች ሰፊ ማብራርያ በፕሮጀክተር በታገዘ መልኩ አቅርበዋል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ የተለያዩ ተቋማት በገብር ኄር ሳምንት የሚሰጡትን አገልግሎት አቅማቸው በሚፈቅደው ልክ ለአረጋውያንና ለተቸገሩ የኅብረተሰባችን ክፍሎች በነጻ ወይም በቅናሽ አገልግሎት እንዲሰጡ ተጠይቀዋል፡፡ ለዚህም መልካም ሀሳብ በጎ ምላሽ የሰጡን ተቋማት በርካታ ሲሆኑ በአስቸኳይ ምላሽ ከሰጡን ተቋማት ውስጥ መራኁት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊቲ ክሊኒክ ተጠቃሽ ሲሆን ላብራቶሪ ምርመራዎቹ ላይ የ5 በመቶ ቅናሽ ለአንድ ሳምንት እንዲሁም አልትራሳውንድ 50 በመቶ ለ3 ወር ቅናሽ ማድረጉን አሳውቋል፡፡
በተጨማሪም ድርጅታችን ገብር ኄር በሀገራችን የተለያዩ ከተሞች የደም ልገሳ መርሀ ግብር አስተባብሮ የደም ልገሳ ተከናውኗል ፡፡ በአዲስ አበባ በመቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ፣ በሰበታ፣ በደሴ፣በደብረ ብርሃን፣ በናዝሬትና በሐዋሳ በተደረገው የደም ማሰባበሰብ ከ200 በላይ ደም መሰብሰብ ተችሏል፡፡ድርጀቱ መሰል መርሃ ግብሮችን አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ዓላማውን የሚደግፉ ድርጅቶችንና ግለሰቦች አብረውት እንዲሠሩ ጥሪውን ያቀርባል።

Post Views: 182