የነፃ ጤና አገልግሎት በዘውዲቱ መሸሻ ሕፃናት እና ቤተሰብ መርጃ በጎ አድራጎት ማኅበር

ገብር ኄር የጤናና ማኅበራዊ በጎ አድራጎት ድርጅት የጤና ክፍል አባላት በዘውዲቱ መሸሻ ሕፃናትና እና ቤተሰብ መርጃ በጎ አድራጎት ማኅበር ቅጥር ግቢ ውስጥ ነሐሴ 22 ቀን በአካል በመገኘት የነፃ ሕክምና አገልግሎት እና ጉብኝት አደረጉ፡፡ በአገልግሎቱ ነርሶች እና የተለያየ ስፔሻሊቲ ያላቸው በተለይም የሕጻናትና የቆዳ ሐኪሞች እንዲሁም ጠቅላላ ሐኪሞች በጠቅላላው ወደ 14 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ በመርኀ ግብሩ ከ40 በላይ ሕጻናትንና የአስተዳደር ሠራተኞች አገልግሎቱን ባሉበት ያገኙ ሲሆን ተጨማሪ ምርመራና እገዛ የሚፈልጉ ታካሚዎች ከተለያዩ ሆስፒታሎች ለማገናኘት ተሞክሯል፡፡ 

የሕክምና አገልግሎቱ እንደተጠናቀቀ አባላቱ ማኅበሩን ዞረው ጎብኝተዋል፡፡ በዚህም ለልጆች የሚሰጠው እርዳታ መጠናከር እንዳለበት እማሆይ ዘውዲቱ መሸሻ አሳስበው መርኀ ግብሩ ተቋጭቷል፡፡ ከዚህም ተያይዞ በዕለቱ ምርመራ ለተደረላቸው ታካሚዎች የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒት ገብር ኄር በራሱ ወጪ ገዝቶ ነሐሴ 28 ቀን አከፋፍሏል፡፡ በቋሚነት ሕክምና የሚያገኙበትንም መንገድ ድርጅታችን እያመቻቸ ይገኛል፡፡   

Post Views: 272